የሆነ ሰው፣ ከሆነ ቦታ የኢሜይል ግንኙነታችንን እየሰለለ/እየተከታተለ (monitoring) እንደሆነ ከጠረጠርን ምን ማድረግ እንችላለን? የመጀመሪያውና ቀላሉ እርምጃ አዲስ የኢሜይል አድራሻ መፍጠር ነው። ይህን ስናደርግ ግን የቀድሞውን ማጥፋት የለብንም፤ እንዲያውም ሰላዩ እየተጠቀምንበት እንዲመስለው ማድረግ አለብን። እንዲህም ሆኖ ግን በቀድሞው የኢሜይል አድራሻችን መልእክት የተለዋወጥናቸው ሰዎች (አድራሻዎች) የስለላ ክትትሉ ኢላማ ተደርገው ሊሆን እንደሚችል መዘንጋት አይገባም። ስለዚህም ተጨማሪ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ አለብን ማለት ነው፤ ለምሳሌ፦

በቅርብ ጊዜ መልእክት የተለዋወጡን ሰዎች ሁሉ እንደ እኛው አዲስ የኢሜይል አድራሻ መክፈት አለባቸው። በተጨማሪም ግንኙነታችንን ከዚህ ቀደም ተጠቅመን ከማናውቀው ቦታ ለምሳሌ ከኢንተርኔት ካፌ ማድረግ ይመረጣል። ይህ አሠራር የሚመከረው የቀድሞ ኮምፒውተራችን ግንኙነቶች በክትትል ስር ከሆኑ አዲሱን የኢንተርኔት አድራሻችንን እንዳያውቁት ለማድረግ ነው። አዲሱን አድራሻ ለመክፈት የግድ የራሳችንን/የቀድሞውን ኮምፒውተር መጠቀም ካለብን ደግሞ በምእራፍ 8፡ ማንነትን መሰወር እና የኢንተርኔት ሳንሱርን ማለፍ ከተጠቀሱት ግንኙነትን የመደበቂያ መሣሪያዎች አንዱን መጠቀም አለብን።

ስለአዲሶቹ የኢሜይል አድራሻዎች እጅግ አስተማማኝ በሆኑ የግንኙነት መስመሮች ብቻ መረጃዎችን መለዋወጥ፤ በአካል ፊት ለፊት ተገናኝቶ መነጋገር፣ ምሥጢራዊነቱ የተጠበቀ የፈጣን መልእክት ወይም ኢንክሪፕት የተደረገ ቪኦአይፒ (VoIP) ብቻ መጠቀም።

በቀድሞ የኢሜይል አድራሻችን የነበሩውን የትራፊክ ፍሰት መጠን ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ እንዳለ እንዲቀጥል ማድረግ። አላማችን ክትትል/ስለላ የሚያደርገው አካል ይህንን አድራሻ አሁንም ስሱ መረጃዎችን ለመለዋወጥ እየተጠቀምንበት እንዲመስለው ማድረግ ነው። እውነተኛ ስሱ መረጃዎቻችንን ሳንገልጥ ነገር ግን ለሰላዩ ትልቅ ነገር የሚመስሉ ነገሮችን መጻጻፍ መቀጠል ይቻላል፤ አድራሻውን መጠቀም ማቆማችን እንዳይታወቅ መጠንቀቅ አይከፋም።

አዲሱ እና የቀድሞው የኢሜይል አድራሻዎች በምንም መንገድ እንዳይገናኙ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። በሁለቱ አድራሻዎች መካከል ፈጽሞ መልእክት መላላክ አይኖርብንም፤ በተመሳሳይም በክትትል ስር ሊሆኑ እንደሚችሉ ለምንጠረጥራቸው ሰዎች መላክ የለብንም።

አዲሱን የኢሜይል አድራሻ መጠቀም ስንጀምር ስለቋንቋ አጠቃቀማችን በሚገባ ማሰብ አለብን። እውነተኛ ስሞችን፣ አድራሻዎችን እና ትኩረት የሚስቡ ቃላትን (በተለይ በእንግሊዝኛ) ለምሳሌ “human rights” ወይም “torture’’ የመሳሰሉትን አለመጠቀም። በምትኩ እነዚህን ቃላት የሚተኩ ሌሎች ኮዶችን በየጊዜው እየፈጠሩ መለዋወጥ ይመከራል።

የኢሜይል ደኅንነት ቴክኒካዊ መከላከያዎችን የማበጀት ጉዳይ ብቻ አይደለም። የእያንዳንዳችን ግላዊ ጥንቃቄ እንዲሁም በኢሜይል ከምንገናኛቸው ሰዎች ጋራ መረጃ የምንለዋወጥበት ወጥ ሥርዓትና ልማድ (ዲሲፕሊን) የደኅንነታችን ሌላው ግብአት ነው።

Facebook Hesabınız Üzerinden Yorum Yapın